ከሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ጋር የኮንክሪት ምሰሶ ኪራይ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የኮንክሪት ምሰሶ ኪራይ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላና የሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር አንዋር ሶውሳ ናቸው፡፡
አቶ ሽፈራው ተሊላ የተፈረመው የምሰሶ ኪራይ ስምምነት የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን ለቴሌኮም አገልግሎት ለመጠቀም እንደሚያስችል ጠቁመው÷መሰረተ-ልማቶችን በጋራ መጠቀም መቻሉ ጥራት ያለውና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡
የኪራይ አገልግሎቱ በሀገሪቱ የተዘረጉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የተቋሙን ገቢ ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
አንዋር ሶውሳ በበኩላቸው÷ የተፈረመው ስምምነት የሁለቱን ተቋማት ሃብት በጋራ ለመጠቀም የሚያስችልና ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው÷ የስምምነቱ ዋና አላማ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተዘረጉ የኤሌክትሪክ የኮንክሪት ፖሎችን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ስምምነቱ ተግባራዊ የሚደረገው በተመረጡ የሀገሪቱ ከተሞች በተተከሉ የኮንክሪት ምሰሶዎች ሲሆን÷ ውሉን የፈረመው ሳፋሪኮም በሚያገኘው አገልግሎት በዓመት 988 ብር ከ70 ሳንቲም ለአንድ ምሰሶ ኪራይ እንደሚከፍል ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተከላቸው የኮንክሪት ምሰሶዎች ኪራይ ተጨማሪ ገቢ ማግኘቱ በእርጅና ምክንያት የወደቁና የዘመሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ማሻሻልና የመልሶ ግንባታ ስራ ማከናወን ያስችለዋል መባሉን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!