Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል እንዲጠናከር ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል በአካባቢው ያለውን የሠላምና ደህንነት የሚመጥን ወቅታዊ አቅም ሊኖረው እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የምስራቅ አፍሪካ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሞች ኮሚቴ ሊቀመንበር ፊልድማርሻል ብርሃኑ ጁላ ናይሮቢ ውስጥ ባደረጉት ንግግር÷ ተጠባባቂ ኃይሉ በአካባቢው ካለው የሠላምና የፀጥታ ሁኔታ ጋር የሚመጥን ቁመናና ዝግጅት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የተጠባባቂ ኃይሉ የያዝነው ዓመት የሁለት ሳምንት ስልጠናትናንት በናይሮቢ ተካሂዷል።
ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይሉ ጥንካሬ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸው÷አባል አገራት የፖለቲካ ቁርጠኝነታቸውንና የሚሰጡትን ድጋፍ እንዲያሳድጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የተቋሙ አባል አገራት ሰልጣኞችን በማሰማራት ላደረጉት አስተዋጽኦ ፊልድማርሻል ብርሃኑ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ሴክሬታሪያት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጌታቸው ሽፈራው በበኩላቸው÷በስልጠናው የተገኘው ልምድ ተጠንቀቅ ኃይሉ ቀደም ሲል የነበረውን አቅም ለማሳደግ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡
በዚሁ የኮማንድ ፖስት ስልጠና ላይ የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ዩጋንዳ፣ ርዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሲሸልስ፣ ኮሞሮስ፣ የአገር መከላከያ፣ የፖሊስ እና የሲቪል አካላት ተሳታፊ መሆናቸውን ተቋሙ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አመላክቷል፡፡
ኤታማዦር ሹሙ ቀደም ሲል ከኬንያ የመከላከያ ሚኒስትር ዩጂን ዋማሉዋ እና ሮበርት ኪቢቾ ጋር በነበራቸው ውይይት ተቋሙን በማጠናከር ረገድ ኢትዮጵያና ኬንያ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ መግባባት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያና ኬንያ በመልካም ብቻ ሳይሆን በአስቸጋሪ ወቅቶችም ጠንካራ ወዳጆች ናቸው ያሉት የኬንያ የመከላከያ ሚኒስትር ዩጂን ዋማሉዋ የአሁኑ ትውልድም ይህን ከፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.