የወልዲያ – ጭፍራ – ሚሌ የ90 ሜትር ድልድይ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በወራሪ ቡድኑ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የወልዲያ-ጭፍራ-ሚሌ የ90 ሜትር ድልድይ ግንባታ ተጠናቆ ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
የዲስትሪክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሳምሶን ተስፋየ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት በደረሰበት ድልድይ ምክንያት መንገድ እንዳይቋረጥ ተቀያሪ መንገድ በመስራት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
በጥቅሉ 20 ሚሊየን ብር የወጣበት ይህ ድልድይ የሀገሪቱ ትልቅ የንግድ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበትና ጠቀሜታው የጎላ ነው። በወራሪ ቡድኑ ከተሰበረ በኋላ አሽከርካሪዎች የዙሪያ 100 ኪሎ ሜትሮች ለመጓዝ፣ ለእንግልትና ለተሽከርካሪ ብልሽት ሲዳረጉ እንደነበር የመንገዱ ተገልጋዮች ነግረውናል።
የብረት ድልድዩ ከባድ ጭነቶች መሸከም የሚችልና ተሽከርካሪዎች ያለ ችግር የሚያልፉበት ራምፕ የተገጠመለት ዘመናዊ ድልድይ መሆኑንም በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድልድይ መሀንዲስ ኢንጅነር ግርማ ወርቁ ተናግረዋል
በወራሪ ቡድኑ ተሰብሮ የነበረው ሌላኛው የውጫሌ ዋና መስመር ድልድይም በ10 ቀናት ውስጥ ተጠናቆ ለተሽከርካሪ ክፍት እንደሚሆንና 90 በመቶ የሚሆነው የግንባታ ሥራም መጠናቀቁን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮምቦልቻ ዲስትሪክት ገልጿል። ድልድዩ 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ወጭ ተደርጎበታል።
ከ50 ሜትር በላይ ጉዳት የደረሰበት ትልቁ የወልዲያ ቆቦ አለውሀ ድልድይ ሌላኛው የግንባታ ሥራ ፕሮጀክት ሲሆን የብረት ድልድዩ ተጠናቆ አገልግሎት መጀመሩም ተመልክቷል፡፡
በአንድነት ናሁሰናይ