የሶማሊያ መሪዎች ለሀገሪቱ የምርጫ ሂደት መቋጫ እንዲያበጁለት ተጠየቁ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሊያ መሪዎች በመነጋገር እና በመግባባት የሀገሪቷን የምርጫ ሂደት እንዲቋጩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጠየቁ፡፡
ከ91 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሀገሪቷ የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በተመራጮች ተይዘው በመጠናቀቃቸው የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ቀሪዎቹ ቦታዎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚሟሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
የሀገሪቷን የተወካዮች ምክር ቤት የማሟያ ምርጫ ሂደት ያላጠናቀቁ ክልሎች ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነሱም ሂርሻቤሌ እና ጁባላንድ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎቹ በቀጣይ በተለይ የጁባላንድ ነዋሪዎች የሚያሰሙትን ድምጽ ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ እና አሁን ላይ ግን በንግግር እና በመመካከር የምርጫ ሂደቱን እንዲያጠናቅቁ መምከራቸውን የዘገበው ሺንዋ ነው፡፡