ህዝቡ አንድነቱን በማጠናከር ከፋፋይ አካሄዶችን በየቤተ እምነቱ ማውገዝና ማጋለጥ አለበት – የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህዝቡ ከመከፋፈል ይልቅ ለብዙ ሺህ ዓመታት በገነባው የአብሮነት እሴት አንድነቱን በማጠናከር ከፋፋይ አካሄዶችን በየቤተ እምነቱ ማውገዝና ማጋለጥ እንደሚገባው የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።
በሰሞኑ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ የአቋም መግለጫ ።
አገራችን ኢትዮጵያ የብሔሮች እና የሃይማኖቶች ብዝሃነት ያለባት ሀገር ነች። እነዚህ ልዩነቶች በአንዳንድ ሀገራት የመለያየት እና የመጠፋፋት መነሻ ሲሆን የኢትዮጵያ ታሪክ ግን ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው።
ኢትዮጵያ ሀገራችን የእስልምና እና የክርስቲና ሃይማኖቶችን አቅፋ የያዘች ሁሉም ሃይማኖቶችን በእኩልነት የምታስተናግድ የሁለቱም እምነት ተከታዮች የየራሳቸውን እምነት ይዘው በቀረው ወንድምና እህት መሆናቸውን አውቀው አንዱ የሌላውን እምነት ሳይጫን በመረዳዳት በመቻቻል አብሮ በመብላትና በመጠጣት ለዓለም ህዝብ ተምሳሌት የሚሆን እሴት ገንብቶ የጋራ ሀገሩን በጋራ ሲገነባና ሲጠብቅ ኖሯል።
የኢትዮጵያ ከፍታ የሚያሰጋቸው አለፍ ሲልም በእኛ ኪሳራ ሲበለጽጉ የነበሩ ጥቅማቸው የሚቀርባቸው ወገኖች ሁሉ ተባብረው አገራችንን ለመበታተን ብዙ ቢጥሩም ህዝባችን በአንድነት በጋራ ቆመንው በመከላከላቸው አልተሳካላቸውም።
ይሁንና በዓለም ህዝብ ፊት የተሸነፉ የውስጥና የውጪ ጠላቶቻችን ከሰሞኑን የሃይማኖቶችን ግጭት በማስነሳት አገራችንን የደም ምድር ለማድረግ፣ ህዝባችንን የሞትና ሰቆቃ ገፈት ቀማሽ እንዲሆን እና እኩይ ሀገር የመበተን ህልማቸውን እውን ለማድረግ ሌተ ቀን እየተረባረቡ ይገኛሉ።
ስለሆነም ህዝባችን ይህንን በመረዳት ከመከፋፈል ይልቅ ለብዙ ሺህ ዓመታት በገነባው በአብሮነት እሴት አንድነቱን ማጠናከር ከከፋፋይ አካሄዶችን በየቤተ እምነቱ ማውገዝና ማጋለጥ ይኖርበታል።
መንግሥታችን የጠላቶቻችን ተልዕኮ በመቀበል በሃይኖት ሰበብ ግጭት ያስነሱትን እንዲሁም እያስፋፉ የሚገኙ ወገኖችን ከህዝቡ ጋር በመሆን አድኖ ለፍርድ እንደሚያቀርባቸው እየተማመንን በሃይማኖት ሽፋን የሚደረግ ማናቸውንም ግጭት ቀስቃሽና አባባሽ ሁኔታ አጥብቀን እንቃወማለን።
እስካሁንም በዚሁ ሰበብ የሰው ህይወትና ንብረት እንዲወድም ያደረጉ ቡድኖችን በጽኑ እናወግዛለን። በሂደቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች መጽናናትን እንመኛለን።
ለእስልምና እምነት ተከታዮች በዚህ አጋጣሚ በድጋሚ እንኳን ለኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ! ኢድ ሙባረክ
የሲዳማ ብ/ከ/መንግሥት
ሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬስ ሴክሬታሪያት
ሚያዝያ 24/2014
ሀዋሳ