አሜሪካ እና ሩሲያ የዩክሬን የወጪ እህል ንግድ ሥምምነት እና የእስረኞች ልውውጥ ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ እና ሩሲያ የዩክሬን የወጪ እህል ንግድ ሥምምነት እና የእስረኞች ልውውጥ ላይ በስልክ መምከራቸው ተገለጸ፡፡
የሥልክ ውይይቱን ያደረጉት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና የአሜሪካ አቻቸው አንቶኒ ብሊንከን መሆናቸውን አር ቲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በአሜሪካ አነሳሽነት የአሜሪካ እና የሩሲያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በእንዲህ ያለ ሁኔታ ሲመክሩ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
ሀገራቱ ከሩሲያ-ዩክሬን ግጭት ይልቅ ባለፈው ሳምንት ቱርክ ላይ የተፈረመውን የዩክሬን የምግብ እህል በወጪ ንግድ ለዓለም ገበያ ማቅረብ በሚያስችለው ስምምነት ላይ ትኩረታቸውን አድርገው መወያየታቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም ሀገራቱ የእስረኞች ልውውጥ ማድረግ በሚችሉበት አግባብ ላይ መምከራቸውም ነው የተዘገበው፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሩሲያ በእስር ላይ የሚገኙት ፓውል ዊላን እና ብሪትኒ ግሪነር በሚለቀቁበት ሁኔታ ላይ ግልጽ እና ቀጥተኛ ውይይት ማድረጋቸውንም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ አንስተዋል፡፡
ኮከብ የቅርጫት ኳስ ተጫዋቿ ብሪትኒ ግሪነር እና የቀድሞ የአሜሪካ የባሕር ኃይል አባል ፖል ዊላን በሩሲያ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ መነገሩ ይታወሳል።
ግሪነር በቁጥጥር ስር የዋለችው በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ወንጀል ተከሳ ሲሆን ዌላን ደግሞ ለአሜሪካ ሰልለሃል በሚል መሆኑን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።
ሩሲያ በአጸፋው አሜሪካ በፈረንጆቹ 2012 ላይ የጦር መሳሪያ አከፋፋይ ነው በሚል ለፈረጀችው አሸባሪ ድርጅት ድጋፍ አድርጓል ፣ ዜጎቼንም ለመግደል አሢሯል በሚል የ25 ዓመታት እስራት የፈረደችበትን ቪክቶር ቦውት የተባለ ተከሳሽ እንድትለቅላት ሳትጠይቅ አይቀርም የሚል ግምት እንዳለ ደግሞ ሲ ኤን ኤን ዘግቧል፡፡