ሩሲያ የኒውክሌር ጣቢያ ቀጠናን ከወታደራዊ ኃይል ነፃ እንድታደርግ የቀረበላትን ጥያቄ ውድቅ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ የደቡባዊ ዩክሬን ዛፖሪዢያ የኒውክሌር ጣቢያ አካባቢን ሙሉ በሙሉ ከወታደራዊ ኃይል ነፃ እንዲታደርግ በተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የቀረበላትን ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች።
ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ውጪ እንዲሆን የሚለው ጥያቄ የቀረበው የአውሮፓ ትልቁ የኑክሊየር ጣቢያ ከሆነው ዛፖሪዢያ አካባቢ ስለተካሄደው ድብደባ ሩሲያና ዩክሬን በየፊናቸው በመወነጃጀል በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት በመባባሱ ነው ተብሏል፡፡
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይህንን ያሉት ትናንት ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እና ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ጋር በላቪቭ ከተማ ከተወያዩ በኋላ ነው፡፡
በኒዩክሌር ጣቢያው ላይ ሊደርስ የሚችል ማንኛውም ጉዳት “ራስን በራስ ማጥፋት ነው” ሲሉ ጉቴሬዝ አስጠንቅቀዋል።
ተቋሙ የወታደራዊ ዘመቻ አካል መሆን የለበትምም ነው ያሉት፡፡
ሩሲያ የኒዩክሊየር ጣቢያውን አካባቢ ለቃ እንድትወጣ መጠየቃቸውም ታውቋል፡፡
ነገር ግን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ጥሪውን ውድቅ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡
የኒዩክሌር ጣቢያው ከወታደራዊ ጥበቃ ውጭ ከሆነ ጣቢያውን ይበልጥ ተጋላጭ ያደርገዋል ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፡፡
በሌላ በኩል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ ሩሲያ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን የያዙና 24 ሰዓት ሙሉ ግዳጅ ለመፈጸም ዝግጁ የሆኑ ሦስት ተዋጊ አውሮፕላኖችን ወደስፍራው በመላክ በተጠንቀቅ ላይ መሆኗ ተዘግቧል፡፡
የመከላከያ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችሉ የሩሲያ ሚግ-31 አውሮፕላኖች በካሊኒንግራድ ክልል በሚገኘው ቻካሎቭስክ አየር ማረፊያ ላይ እንደሰፈሩ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ትናንት ማሳወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ዛፖሪዢያ የሚገኘው የአውሮፓ ግዙፉ የኑክሌር ጣቢያ ከመጋቢት ወር ጀምሮ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር መሆኑ ይታወሳል፡፡