Fana: At a Speed of Life!

ዋጎች በየዘመኑ ያጋጠማቸውን ከባድ ችግር በጀግንነት አልፈዋል- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዋጎች በየዘመኑ ያጋጠማቸውን ከባድ ችግር በጀግንነት አልፈዋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
“ሻደይ” የልጃገረዶች በዓል በሰቆጣ ከተማ እየተከበረ ይገኛል፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን በሰቆጣ እየተከበረ በሚገኘው የሻደይ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ዋጎች በየዘመኑ ያጋጠማቸውን ከባድ ችግር በጀግንነት ማለፍ ችለዋል፤ ለዚህ ደግሞ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በአሸባሪው ህወሓት ያጋጠማቸውን ከባድ ችግር በፅናትና በጀግንነት ማለፋቸው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ህወሓት በዋግ ሕዝብ ላይ ባደረሰው ዘርፈ ብዙ ጉዳት÷ የሕይወት መስዋዕትነት፣ የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት የደረሰባችሁ ለኢትዮጵያ የከፈላችሁት በመሆኑ ትልቅ ምስጋና ይገባችኋልም ነው ያሉት።
አሸባሪው ህወሓት በጦርነትና በሕጻናት መስዋዕትነት መኖር የለመደ መሆኑን ጠቅሰው÷ አሁንም የጦርነት ጉሰማ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ሰላማዊ መፍትሄዎችን በመፈለግ የተለያዩ መንገዶችን ተጉዟል ያሉት አቶ ደመቀ÷ ህወሓት ግን የሰላም እድል እያሳጣ ለጦርነት ለዳግም ሌላ ጥፋትና ውድመት እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት አሁንም ቢሆን ለሰላም ያለው አቋም እንደፀና መሆኑን አረጋግጠው÷ ለሰላም አማራጭ ያለውን ኃላፊነት እስከ ጥግ ድረስ በመሄድ ኃላፊነቱን ይወጣል ነው ያሉት አቶ ደመቀ፡፡
ካሁን በኋላ ወደ ዳግም ጦርነት ከመግባት ይልቅ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ የትግራይ ሕዝብም የሰላም መንገዱ እንዲሳካ ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስት ቁጭ ብለን በመነጋገር የተቋረጡ አገልግሎቶችን ለሕዝቡ መመለስ ያስፈልጋል ብሎ ለህወሓት እድል ቢሰጥም አሸባሪው ቡድን ግን ይን እያደረገ አለመሆኑንም አስረድተዋል።
አሁንም በወረራ የያዛቸው ቦታዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ እነዚህን ቦታዎች በፍጥነት ለቆ ወደሰላማዊ ድርድር እንዲመለስ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ በሻደይ አከባበር ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ከአሸባሪ ሃይሎች የተቃጣብንን ወረራ በመቀልበስ አንድነታችንን እናጠናክራለን ብለዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ባደረገው ወረራ ባለፈው አመት የ”ሻደይ” በዓል እንዳልተከበረ ጠቁመው ዛሬ ግን ወረራውን ቀልብሰን በዚህ መልክ ልናከብር ችለናል ብለዋል፡፡
የሀገር መከላከያ፣ የአማራ ልዩ ሀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ እንዲሁም መላው ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ትግል ወረራውን ቀልብሰን ሻደይን በዚህ መልክ ማክበር ችለናል ለዚህም የድርሻቸውን ለተወጡ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
አሁንም የተቃጣብንን ወረራ በመቀልበስ አንድነታችንን እናጠናክራለን ነው ያሉት ፡፡
የሻደይ በዓል የልጃገረዶች የደስታ፣ የብሩህ ተስፋ በዓል ነው፤ይህን የቱሪዝም መስህብ ለዓለም ህዝብ ማሳየት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በተመሳሳይ የ”አሸንድየ” እና “ሶለል” በዓል በላሊበላ እና በቆቦ ከተማ እየተከበረ ይገኛል፡፡
በታሪኩ ለገሰ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.