ዶክተር ሊያ ታደሰ “በጎነት ለጤናችን” አገልግሎትን በሰቆጣ ከተማ አስጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ “በጎነት ለጤናችን” በሚል የተዘጋጀው የክረምት የበጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት መረሐ ግብር ዛሬ በአማራ ክልል ሰቆጣ ከተማ አስጀመሩ።
ሚኒስትሯ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ በክረምቱ መርሐ ግብር የነፃ ህክምና አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ከፍለው መታከም ለማይችሉ 100 ሺህ ዜጎች የጤና አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱን ጠቅሰው፥ ከሻደይ በዓል ጋር ተያይዞ በሰቆጣ ከተማ የተጀመረው መረሐ ግብር ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተጀመረው የክረምት የጤና አገልግሎት በክልሉ 20 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ዶክተር መልካሙ፥ መርሐ ግብሩ ለጤና አገልግሎት መሻሻል አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።