የህዳሴው ግድብ ለልማት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው- አምባሳደር ስለሺ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድነታችን ድንቅ ማሳያና ለልማት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ተናገሩ፡፡
በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያና የምስጋና ስነ ስርዓት ተካሄዷል።
በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ለግድቡ ግንባታ የሚውል ከ70 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ተሰብስቧል፡፡
ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀው “ማይ ገርድ ዶት ኮም” (www.mygerd.com) ድረ-ገጽ የተሰበሰበው 310 ሺህ ዶላርም ለመንግሥት ገቢ ተደርጓል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በውግንና፣ በማህበራዊ ትስሰር ገጾች ቅስቀሳ፣ በምርምርና በተለያዩ መስኮች እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነታችን ድንቅ ማሳያና ለልማት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው” ያሉት አምባሳደሩ፥ ሁሉም አካል ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድጋፉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው፥ የህዳሴ ግድብን ዘርፈ ብዙ ጥቅም የኢትዮጵያን የለውጥና እድገት ህልሞች ለማሳካት ልናውለው ይገባል ብለዋል።
ተሳታፊዎችም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉት ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!