Fana: At a Speed of Life!

የሀረሪ ክልል አሸባሪው የህውሃት ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀረሪ ክልል አሸባሪው የህውሃት ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት በወቅታዊ ክልላዊ የጸጥታ ጉዳዮች ተወያይቶ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫው እንደተመላከተው ምክር ቤቱ በክልሉ የተከናወኑ የሠላምና ጸጥታ ሥራዎች ፍሬያማ መሆናቸውን የገመገመ ሲሆን፥ በቀጣይም በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብሏል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ሰላም ወዳዱ የክልሉ ህዝብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት እና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ዛሬም እንደ ትላንቱ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል።
እንዲሁም አሸባሪው የህውሃት ቡድን የፌደራል መንግስቱ ለሰላም ያሳየውን ዝግጁነትና ያቀረበውን ጥሪ ወደ ጎን በመተው ጦርነት በመጀመሩ የትግራይ ክልል ሕዝብና በተለይም ወጣቶችን ለጦርነት እየማገደ እና በአጎራባች ክልሎች የለመደበትን ጥቃት እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ስለሆነም የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት የፌደራል መንግስት ለሰላም ያሳየውን ቁርጠኝነት እና ተጨባጭ እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ የመደገፉ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ አሸባሪው የህውሃት ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁነቱን ገልጿል፡፡
ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ከሀረሪ ክልል የፀጥታው ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
የሀረሪ ክልል የፀጥታው ምክር ቤት በወቅታዊ ክልላዊ የጸጥታ ጉዳዮች ተወያይቷል።
በሀረሪ ክልል እየተስተዋለ የሚገኘው አንፃራዊ ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ የፀጥታ ሀይል ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ሀይል እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ይገኛል።
ምክር ቤቱ በክልሉ የተከናወኑ የሠላምና ጸጥታ ሥራዎች ፍሬያማ መሆናቸውን የገመገመ ሲሆን በቀጣይም በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
በተለይም የህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ህገ ወጥ ግንባታ፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ኮንትሮባንድን እና ህገ ወጥ ንግድን ከመቆጣጠር አንፃር እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ይበልጥ በማጠናከር ህዝብን ባሳተፈ መልኩ በቁርጠኝነት ይሰራል።
ከዚህ በተጨማሪም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆኖ የጥፋት ተልእኮ የሚፈጽሙ አካላትን በማጥራት የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ በትኩረት የሚሰራ ይሆናል።
በክልሉ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር የኑሮ ውድነት እንዲባባስ በሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች እና በመልካም አስተዳደር ችግር ህዝብን የሚያማርሩ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በመግለጫው አመላክቷል።
ከዚህ በተጨማሪ የማህበራዊ ሚዲያን ለእኩይ ዓላማ በማዋል ህዝብን ከመንግሥት የሚያጋጩ መልዕክቶችን በመቅረጽ የሚያሰራጩና፣ እምነትን መነሻ በማድረግ ግጭት የሚቀሰቅሱ አካላት እንዲሁም እውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ በየማህበራዊ ሚዲያዉ የሚደረግ ዘመቻ የፀጥታ ምክር ቤቱ በምንም መልኩ እንደማይታገስ ያስታውቃል።
ሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት እና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ዛሬም እንደ ትላንቱ የክልላችን ህዝቦች ለሰላም ዘብ እንዲቆም ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል።
አሸባሪው የህውሃት ቡድን የፌደራል መንግስቱ ለሰላም ያሳየውን ዝግጁነትና ያቀረበውን ጥሪ ወደ ጎን በመተው ጦርነት በመጀመሩ የትግራይ ክልል ሕዝብና በተለይም ወጣቶችን ለጦርነት እየማገደ እና በአጎራባች ክልሎች የለመደበትን ጥቃት እያደረሰ ይገኛል።
ስለሆነም የክልሉ ፀጥታ ም/ቤት የፌደራል መንግስት ለሰላም ያሳየውን ቁርጠኝነት እና ተጨባጭ እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ የመደገፉ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ አሸባሪው የህውሃት ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁነት ለመግለፅ ይወዳል።
የሀረሪ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት
ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም
ሀረር
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.