አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ከደቡብ ኮሪያና ከዓለም ዓቀፉ የምግብ ድርጅት ልዑካን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ከደቡብ ኮሪያና ከዓለም ዓቀፉ የምግብ ድርጅት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ከደቡብ ኮሪያ ፓርላማ አባላትና ከዓለም ዓቀፍ የምግብ ድርጅት ከተውጣጡ ከፍተኛ የአመራር ልዑካን ቡድን ጋር በክልሉ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ ላይ መክረዋል።
በተጨማሪም በደቡብ ኮሪያ ፓርላማ አባል ጃጁንግ ሊ ለተመራው የዓለም ምግብ ድርጅት እና የደቡብ ኮሪያ መንግስት ባለስልጣናት ለተፈናቃይ ወገኖች ስለሚደረገው ድጋፍ አቶ ሙስጠፌ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ ፓርላማ አባላትና የዓለም ምግብ ድርጅት ባለስልጣናት በበኩላቸው÷ የክልሉ መንግስት ለተፈናቃዮች የሚያደርገው የአስቸኳይ ምግብ ድጋፍ ጥረት አበረታች መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለዜጎች በሚደረገው ድጋፍ የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ጠቅሰው÷ ከሶማሌ ክልል መንግስት ጋር በዘላቂ ልማት ስራዎች ላይ እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡