በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተከፈተውን ጦርነት በተባበረ ክንድ መቀልበስ ይገባል- ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር ሉዓላዊነት ላይ አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት በተባበረ ክንድ መቀልበስ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ÷በሀገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከክልል አስከ ወረዳ ካሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ÷መንግስት ሠላምን አማራጭ አድርጎ ቢንቀሳቀስም አሸባሪው ህወሓት ጦርነትን በመምረጥ ሀገርን ለመበታተን ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት መክፈቱን አስታውሰዋል፡፡
ውስጣዊ አንድነትን የበለጠ በማጠናከር ሀገርን ለማዳን የአመራሩ ኃላፊነት ከፍተኛ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በበኩላቸው÷ መንግስት ተገዶ የጀመረው ጦርነት በድል ተጠናቆ የሀገሪቱ ሠላም ወደ ቀድሞ እንዲመለስ አመራሩ ቁርጠኛ መሆን ይገባዋል ነው ያሉት።
ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር መሥራት ከሁሉም እንደሚጠበቅም ጠቁመው ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችንም የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡