83 ተጋላጭ ፍልሰተኞችን ከጂቡቲ ወደ ሀገራቸው መለሰ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2014፣ (ኤፍ ቢ ሲ) በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዚያው ከሚገኘውዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ቢሮ ጋር በመተባበር በሣምንቱ ውስጥ 83 ፍልሰተኞችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አደረገ፡፡
ኤምባሲው ለፍልሰተኞቹ የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀትና ግንዛቤ በማስጨበጥ ነው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያደረገው።
ከፍልሰተኞች መካከል ከፊሎቹ ከየመን ወደ ጂቡቲ የገቡ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመሻገር ጂቡቲ ከገቡ በኋላ ባህር የመሻገር ሀሳባቸውን የቀየሩ ናቸው ተብሏል፡፡
ፍልሰተኞቹ በኅገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በመካከኛው ምሥራቅ ሀገራት በአጭር ጊዜ ለመክበር በሚል ቀቢጸ ተሥፋ ተታልለው ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ከሀገራቸው የወጡ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ፍልሰተኞቹ በመሸጋገሪያና መዳረሻ ሀገራት ለውሃ ጥም፣ ረሃብ፣ ለጤና መታወክ፣ ለከፍተኛ እንግልትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች መዳረጋቸውን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል፡፡
ከኢትዮጵያ-ጂቡቲ-የመን የሚደረገው ኅገ-ወጥ የሰዎች ፍልሰት በአደጋዎች የተሞላ መሆኑ ይነገራል፡፡
ለአብነትም ባለፉት ሦስት ዓመታት ከጂቡቲ በመነሳት ቀይ ባሕርን በማቋረጥ ላይ እያሉ ሥድስት ኅገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች የጀልባ መገልበጥ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡
በአደጋውም ከ118 በላይ ኢትዮጵያውያን ለኅልፈት መዳረጋቸው ነው የተገለጸው፡፡
የጂቡቲ የባሕር ጥበቃ ኃይል ባለፉት ሥድስት ወራት ብቻ ከ561 በላይ ፍልሰተኛ ዜጎችንን ጭነው ከጂቡቲ ወደ የመን የሚጓዙ ኅገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ጀልባዎችን በመያዝ ፍልሰተኞችን ታድጓል፡፡
ከጂቡቲ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚወስደው የፍልሰት መስመር ለሥነ-ልቦናና አካላዊ ጉዳት እንዲሁም ሞት የሚያጋልጥ በመሆኑ ዜጎች በኅገ-ወጥ ደላሎች ተታለው ውድ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ እንዳይጥሉና ከሀገራቸው እንዳይወጡ ኤምባሲው መልዕክቱን አስተላልፏል።