በአንኮበር ወረዳ እናትና ልጅ በደራሽ ውሃ ተወስደው ህይወታቸው አለፈ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ሸዋ ዞን በአንኮበር ወረዳ እናትና ልጅ በደራሽ ውሃ ተወስደው ህይወታቸው ማለፉን የወረዳው ፖሊስ አስታወቀ።
የእናትና ልጁ ህይወት ያለፈው አይራራ የተባለውን ወንዝ ሲያቋርጡ ነው ተብሏል።
አደጋው የደረሰው ዛሬ ከማለዳው 12 ሰዓት ሲሆን፦ የወደራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት እናትና ልጅ ወደ አልዩ አምባ ከተማ ሲያመሩ ነው በደራሽ ውሃ ተወስደው ህይወታቸው ያለፈው።
የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ኮማንደር ፍስሃ ዘነበ እንዳሉት አደጋው የደረሰባቸው እናት አልዩ አምባ ከተማ የምትማረውን ተማሪ ልጃቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ ስንቅ ጭነው እየተጓዙ ነበር።
የእናትና ልጅ አስክሬን እስካሁን አልተገኘም ያሉት ኮማንደር ፍስሃ ህብረተሰቡ በፍለጋ ላይ መሆኑን ነግረውናል።
በሳምራዊት የስጋት