የልብ ህመም መንስኤ እና ህክምናው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ልብ ኦክስጂን ያለውን ደም መርጨት ዋነኛ ተግባሩ የሆነ የሰውነታችን ክፍል ነው፡፡
ልብ ደምን የሚረጨው በመኮማተር እና በመዘርጋት መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልብ ሀኪም ዶክተር ደጁማ ያዴታ ተናግረዋል፡፡
የዚህ መስተጓጎልም ብዙ አይነት ምልክቶችን እንደሚያመጣ ገልፀዋል፡፡
ሰውነት ማድረግ ሚችለውን እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻል፣ የድካም ስሜት፣ ማዞር፣ እየከፋ ሲሄድ ደግሞ የተለያዩ የሰውነት አካላችን መስራት አለመቻል ለምሳሌም ኩላሊት በደንብ እንዳያጣራ ማድረግ የልብ ህመም ምልክቶች መሆናቸውን ይገልጻሉ።
እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የልብ ምት መጨመር፣ እንደ ድንገት ደረት ላይ ውጋት መሰማት፣ ከኢንፌክሺን ጋር የተያያዘ ከሆነ ደግሞ ትኩሳት ምልክቶቹ ናቸው ብለዋል የህክምና ባለሙያው፡፡
የልብ ህመም አይነቶቹን በተመለከተም ከመንስዔ አንፃር በተፈጥሮ የሚመጣ እና ከውልደት በኋላ የሚመጡ እንዳሉ የገለፁት ዶክተር ደጁማ፥ ለበሽታው ከሚያጋልጡ ነገሮች አንፃርም የተለያየ አይነት የልብ ሕመም እንደለ ጠቁመዋል፡፡
የልብ ህመም አጋላጭ መንስዔዎቹም በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰው የጉሮሮ ቁስለት፣ ጨውና ቅባት የበዛበት ምግብ መመገብ ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ጫት መቃም ፣ከመጠን በላይ መጠጥ መጠጣት ጥቂቶቹ ናቸው ብለዋል፡፡
መከላከያውም የጉሮሮ ኢንፌክሽን ሲኖር ቶሎ መታከም ፣ ልጅን ጤናማ በሆነ አመጋገብ ማሳደግ፣ ተከታታይ የጤና ምርመራ ማድረግና እንደ ኮሌስትሮል ፣ የደም ግፊትና ስኳር ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ።
ህክምናውን በተመለከተ ደግሞ ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ከታዩ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ መታከም እንደሚያስፈልግም ነው የሚመክሩት።
በሚደረጉ ምርመራዎች የልብ ህመም አይነቶች ከተለዩ በኋላ ከዚያ በመነሳት ህክምናው ይሰጣልም ነው ያሉት፡፡