Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ኬንያ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር አደጋ እንዳያስከትል አመራሮች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል- አቶ ርስቱ ይርዳ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ኬንያ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ኃይል ለመስጠት እንዲችል እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮች በፍጥነት እልባት እንዲሰጣቸው የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ አሳሰቡ፡፡

አቶ ርስቱ እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መስመሩ ኃይል ማስተላለፍ ሊጀመር መሆኑን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኮንስትራክሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ክብሮም ካህሳይ ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የግንባታ ሂደቱና የደረሰበት ደረጃ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ስለተፈረመው የኃይል ሽያጭ ውል እና ፕሮጀክቱ ስላለው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ ገለጻ ተደርጓል፡፡

መስመሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች በህገ ወጥ መንገድ በወረራ የተገነቡ አዳዲስ ቤቶች መኖራቸውን፣ ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው በወረዳና በከተማ አስተዳደሮች ቤቶቹ እንዲነሱ አለመደረጋቸው ተመላክቷል፡፡

በኃይል ማስተላለፊያ ግዙፍ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈፀመውን ስርቆት ማስቆም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡

መስመሩ በቅርቡ ኃይል ማስተላለፍ ስለሚጀምር ህብረተሰቡ ከታወር ንክኪ እንዲርቅ እና እንዲጠነቀቅ በክልሉ የአስተዳደር መዋቅር ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተጠይቋል፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተደዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ÷ መስመሩ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ሥራ ሲጀምር የተጠቀሱት ችግሮች በፍጥነት ካልተቀረፉ ከፍተኛ አደጋ ስለሚያስከትል በየደረጃው ያሉ አመራሮች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም ለህብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንዲሰራ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በመስመሩ ላይ ኤሌክትሪክ ስለሚለቀቅ ለጥንቃቄ ብቻ ሳይሆን ስርቆትን አስመልክቶም ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

በህጋዊ መንገድ ከይዞታቸው ለሚነሱት ተነሺዎች በአጭር ቀናት ውስጥ ቦታ እንዲዘጋጅ፣ መነሳት ያለባቸውም እንዲነሱና ጉዳዮን የሚከታተል ግብረ ኃይል በፍጥነት እንዲቋቋም አቅጣጫ ማስቀመጣቸውንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.