አቶ ደመቀ መኮንን ከዩኒስኮ እና ከዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ሪታ ቢሶናውት እና የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም (ኦ ኢ ሲ) ዋና ፀሐፊ ሼክ መንሱር ሙሳላምን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የዩኔስኮ ዳይሬክተር ሪታ ቢስናውዝ እና ከዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም ዋና ጸሃፊ ሼክ ማንሱር ቢን ሙሳላም ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚህም ወቅት ኢትዮጵያ ሀገራዊ ቅርሶቿን ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት ዩኔስኮ እያደረገ ላለው ቀጣይነት ያለው የቴክኒክ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በበኩላቸው፥ ሁለቱ ወገኖች ትምህርትን፣ ባህልንና ሳይንስን በማስፋፋት ረገድ ግንኙነታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል ብለዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም ዋና ጸሃፊ ከሆኑት ሼክ ማንሱር ቢን ሙሳሌም ጋርም ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ በነበራቸው ቆይታም ኢትዮጵያ የድርጅቱ ዋና መቀመጫ ተደርጋ በመመረጧ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው ለድርጅቱ አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር እና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ በበኩላቸው፥ ድርጅቱ መቀመጫውን ኢትዮጵያ ማድረጉ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት በመጥቀስ ለድርጅቱ ስኬታማነት የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ እንደማይለየው ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡