በበዓላቱ ከእርድ የሚገኘውን ቆዳ በጥንቃቄ በማዘጋጀት በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ ይገባል
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጪዎቹ የገና እና ጥምቀት በዓላት ከሚፈጸም እርድ የሚገኘውን ቆዳ በጥንቃቄ ለገበያ ማቅረብ እንደሚገባ የቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምር እና ልማት ማዕከል አሳሰበ።
የማዕከሉ ተወካይ ስራ አስኪያጅ አቶ መሃመድ ሁሴን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ቆዳና ሌጦ ለዘርፉ አምራች ኢንተርፕራይዞች፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡
ለቆዳ ጥራት መቀነስ ዋነኛው ምክንያት በእርድ ወቅት በቢላዋ በቆዳው ላይ የሚደርስ ጉዳት እና በጊዜ ለገበያ አለመቅረብ መሆኑን አቶ መሃመድ ጠቁመዋል፡፡
ስለሆነም በቀጣዮቹ የገና እና የጥምቀት በዓላት በሚከናወን እርድ ወቅት ማህበረሰቡ ለቆዳ ጥራት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ25 ሚሊየን በላይ እንስሳት ለእርድ ይቀርባሉ ያሉት አቶ መሃመድ ÷ ከዚህ ውስጥም 25 በመቶው ብቻ ለገበያ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል።
ለዚህም በአቅራቢዎች እና ተረካቢዎች መካከል ያለው የገበያ ትስስር አነስተኛ መሆን እና የግንዛቤ እጥረት ዋነኛ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ችግሩን ለመቅረፍም በየአካባቢው የቆዳ መሰብሰቢያ ማዕከላት መኖራቸውን ጠቁመው÷ ህብረተሰቡ ቆዳዎችን በጥንቃቄ በማዘጋጀት በወቅቱ ለገዢዎች ማቅረብ አለበት ብለዋል።
ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሻሻልም በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ