የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
ምክር ቤቱ በፌዴራል መንግስት የግዢና ንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወያየ ሲሆን በአፈጸጸም ሲያጋጥሙ የነበሩና ለመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ የአሰራር ጉድለቶችን ለማረም፣ የተቋማትን ሃላፊነትና ተጠያቂነት የሚያጎለብት፤ የግዢና ንብረት አስተዳደር ስርዓትን በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን አንዲሁም የሀገር ውስጥ አምራቾች በመንግስት ግዢዎች ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ምርታማነታቸው እንዲያድግ ማገዝ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል እንዲጸድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወሰኗል፡፡
በተጨማሪም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ረቂቅ ደንብ ላይ ባደረገው ውይይት በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድጎን አዋጅ ቁጥር (1273/2014 ጠቅለል ባለ መልኩ የተደነገጉ ጉዳዮችን በተለይም የፋይናንስ ጉድለት አሸፋፈን፣ የስጋት መቀነሻ ስልቶች እና በተለያዩ እርከኖች ሊኖር የሚገባውን የቋት ከፍፍል በሚመለከት በዝርዝር መደንገግ በማስፈለጉ አዋጁን ተከትሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የአፈጻጸም ስርዓት እንዲኖር በማድረግ የመድኅን ስርዓቱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን ምከር ቤቱም በደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችንበማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
ከዚህ ባለፈም ምክር ቤቱ በማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ ላይ መወያየቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
በዚህም ማዕድናት የማይታደሱ የተፈጥሮ ሀብቶች በመሆናቸው መጭውን ትውልድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል፣ በአካባቢ ጥቢቃ መርሆዎች ላይ የተመሰረተና ከስነ-ምህዳር ጋር የሚጣጣም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ውጤታማ የሆነ የማዕድን ሀብት አስተዳደር እና ቁጥጥር ሥርዓት የሚዘረጋ፣ ከውጭ የሚገቡ የማእድን ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት፣ውጭ በመላከ የሚገኝ የውጭ ምገዛሪ ገቢን ለማሳደግ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያግዝ፣ በአጠቃላይ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሚኖረውን አስተዋጽኦ ማሳደግ በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡