Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካ ኤምባሲ ለአፋር ክልል 10 ተሽከርካሪዎችን ለገሰ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ መንግሥት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምበሲው በኩል ለአፋር ክልል ፖሊስ አገልግሎት የሚውሉ 10 ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን በስጦታ አበርክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግሥት ጉዳይ ፈፃሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን÷ የተሸከርካሪዎችን ቁልፍ ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ አስረክበዋል፡፡

ለአፋር ክልል ፖሊስ የተደረገው የተሽከርካሪ ድጋፍ በአፋር ክልል አልፎ ወደ ትግራይ የሚጓጓዘውን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በማጀብ ተደራሽነቱን አስተማማኝ ለማድረግ አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ወዲህ በአካባቢው በርካታ አዎንታዊ ለውጦች መታየታቸውንም አምባሳደሯ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በቀጣይ ዘላቂ የሆነው የሰላም ሂደት ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

ለበርካታ ማህበረሰቦች የሚያስፈልገው ከፍተኛ የሰብዓዊ ቁሶች አቅርቦት ተደራሽ እየተደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

በትግራይ፣ አማራና አፋር መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለሚጠባበቁ  ዜጎች የመልሶ ግንባታዎችን በማፋጠን አገልግሎቱ ተደራሽ እየተደረገ ነው ያሉት አምባሳደሯ÷ አሁን ላይ የመልሶ ማቋቋም፣ ትጥቅ ማስፈታትና የማቀራረብ ስራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ አመላክተዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ እየተከናወኑ ያሉ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰው÷  አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥትእና ሕዝብ ጎን በጽናት እንደሚቆምም ነው ያረጋገጡት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.