Fana: At a Speed of Life!

በሲዳማ በሙስና ወንጀል የተከሰሱ 136 አመራሮችና ባለሙያዎች በእስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል በሙስና ወንጀል የተከሰሱ 136 አመራሮችና ባለሙያዎች እስከ 11 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታውቋል።

በክልሉ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ የተመዘበረ የመንግስትና የሕዝብ ሃብት ማስመለስ መቻሉም ነው የተገለጸው፡፡

የሲዳማ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዋና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ማቶ ማሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ÷ ሙስናና ብልሹ አሰራር ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ እንዳይቀጥል  እየተሰራ ነው።

የክልሉ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የፀረ ሙስና ክልላዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ባደረገው እንቅስቃሴ ውጤት መገኘቱን ጠቁመው÷”በዚህም 118 ጥቆማዎች ከህብረተሰቡ ለመሰብሰብ ተችሏል” ብለዋል።

ጥቆማዎቹ በገቢ፣ በፋይናንስና በመንግሥት ቤቶች አስተዳደር እንዲሁም ከኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጥና ከመሬት ጋር በተያያዘ ሙስናና ብልሹ አሰራር መፈጸማቸውን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፀረ ሙስና ክልላዊ ኮሚቴው በ265 መዝገቦች አደራጅቶ ምርመራና ክስ መመስረቱን የገለፁት ሃላፊው÷ ከነዚህ መዝገቦች ውስጥ 72 መዝገቦች በፍ/ ቤት ውሳኔ አግኝተዋል ብለዋል።

በምርመራ ሂደት 505 አመራሮች እና ባለሙያዎች እንዲጠየቁ ተለይተው እስካሁን በ136ቱ ላይ ከአንድ ዓመት እስከ 11 ዓመት በሚደርስ የእስር ቅጣት እንዲቀጡ መወሰኑን ገልጸዋል።

ከእስራት በተጨማሪ የተመዘበረ የሕዝብ ሃብት ለማስመለስ በተደረገ ርብርብ ባለፉት ሦስት ወራት በክስና ምርመራ ሂደት ውስጥ በአጠቃላይ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ የተመዘበረ ሃብት እንዲመልሱ መደረጉንም አንስተዋል።

የእስር ቅጣት የተፈረደባቸው በክልል፣ በወረዳና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ናቸው መባሉን ከክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.