ዩክሬን ለምትፈፅመው ጥቃት አሜሪካ ይሁንታ ሠጥታለች ስትል ሩሲያ ወቀሰች
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩክሬን በሩሲያዋ ክሬሚያ ላይ ያደረሰችውን ጥቃት አሜሪካ በዝምታ መመልከቷን ይሁንታ እንደመሥጠት እንደምትቆጥረው ሩሲያ አስታወቀች፡፡
በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭ በሠጡት ማስጠንቀቂያ አዘል አስተያየት ÷ ዩክሬን በክሬሚያ ሰርጥ አካባቢ የፈጸመችውን ጥቃት ሩሲያ በሁሉም የሀገሪቷ ክልሎች ላይ ሁሉ እንደፈጸመችው ትቆጥረዋለች ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ አስተያየታቸውን የሰጡት ዩክሬን ክሬሚያን መምታቷን ተከትሎ የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን በጉዳዩ ላይ ተቃውሞ ባለማሰማታቸው መሆኑን አር ቲ ዘግቧል፡፡
የደኅንነት አማካሪው ከሲ ኤን ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ÷ “ዩክሬን ሩሲያን እንድታጠቃ ፈቃድም ሆነ ክልከላ አንጥልም ፤ ነገር ግን ዩክሬን ከአሜሪካ ፈቃድ ወስዳ ሩሲያን እንድታጠቃ አናደርግም” ማለታቸው ተጠቁሟል፡፡
አናቶሊ በበኩላቸው ዩክሬን በአሜሪካ እና በሌሎች ምዕራባውያን የጦር መሣሪያዎች በመታገዝ ክሬሚያን ደብድባለች ፤ ይህም ያለ ቅድመ-ሁኔታ ፈቃድ እንደመሥጠት ይቆጠራል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ምዕራባውያኑ ለዩክሬን ኤፍ -16 ተዋጊ ጀት እንዲያቀርቡ ከአሜሪካ ይሁንታ ማግኘታቸው አሜሪካ የሠላም ፍላጎት እንደሌላት የሚያመላክት ነው ሲሉም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ይሄ ሁሉ ተደምሮ ሩሲያ ዩክሬን ላይ እየወሰደች ያለችው ወታደራዊ እርምጃ ትክክል ነውም ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ባለፈው ቅዳሜ ፕሬዚዳንት ባይደን በቡድን ሰባት አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ አጋር ሀገራት ከአሜሪካ የገዟቸውን ኤፍ 16 ተዋጊ ጄቶች ለዩክሬን ቢያቀርቡ ዋሺንግተን እንቅፋት አትሆንባችሁም በሚል ይሁንታ እንደሰጧቸው ገልጸው ነበር።