የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 25 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ለትግራይ ክልል አስረከበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ 25 ሚሊየን ብር የሚገመቱ ምርጥ ዘርና የምግብ እህል ድጋፎችን ለትግራይ ክልል አስረክቧል።
ድጋፉን ያስረከቡት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋየ ማሞና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ አለባቸው ናቸው።
ድጋፉ 10 ሚሊየን ብር ጥሬ ገንዘብና 15 ሚሊየን ብር ግምት ያለው 2 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር፣ ዱቄትና ቦቆሎ መሆኑን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ ፀጋየ ማሞ ገልጸዋል።
የክልሉ ሕዝብና መንግስት ለትግራይ ክልል ያደረገው ድጋፍ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አለመሆኑን ገልጸው÷ በቀጣይ ክልሉን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች የተረከቡትን ድጋፍ በፍጥነትና በፍትሃዊነት ለተጠቃሚው እንደሚያደርሱ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ እያሱ አብረሃ (ዶ/ር)÷ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።