ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም የመጀመሪያ ልዩ ጉባዔውን በኢትዮጵያ ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም (ኦኢሲ) የመጀመሪያ ልዩ ጉባዔውን ዛሬ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም ዋና ፀሐፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም፣ የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት፣ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ጉባዔው በትምህርቱ ዘርፍ እኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና አጋርነት መሰረተ ያደረገ አዲስ የባለ ብዙ ወገን ትብብር መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የፖሊሲ ውይይቶች እና ክርክሮች የሚደረጉበት መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ጉባዔው ዛሬን ጨምሮ ለአራት ቀናት ሲቆይ ለሁለት ቀናት በሚኒስትሮች ደረጃ የሚካሄድ ሲሆን÷ በቀሪዎቹ ቀናት የተቋሙ አባል አገራት መሪዎች ምክክር እንደሚያደርጉ ከወጣው መርሐ-ግብር ለመረዳት ተችሏል።
ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም በፈረንጆቹ ጥር 2020 የተቋቋመ ሲሆን÷ ከአፍሪካ ፣ እስያ፣ ፓሲፊክ፣ ላቲን አሜሪካ፣ ካሪቢያን እና የአረቡ ዓለም አገራትን በአባልነት ያቀፈ ነው።
ኢትዮጵያ የተቋሙ መስራች አባል እና ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫም ናት።
ኦኢሲ ሚዛናዊ እና ሁሉን አቀፍ የትምህርት ስርዓት በመዘርጋት በእኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና አጋርነት ላይ የተመሰረተ ልማት ማምጣትን ዋና አላማው አድርጎ እየሰራ ይገኛል።