Fana: At a Speed of Life!

ከቡና ወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና ምርት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር ÷ የውጭ ምንዛሬ ገቢው የተገኘው በ2015 በጀት ዓመት ከ240 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቡና የተላከባቸው ሀገራትም ሳዑዲ-ዓረቢያ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ኮሪያ፣ ቤልጂየም፣ ጃፓንና ዩናይትድ ዓረብ ኢምሬትስ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ገቢ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ቢኖረውም ከዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ መቀዛቀዝና የዋጋ መቀነስ እንዲሁም ከነበሩት ፈታኝ ሁኔታዎች አንጻር የሚበረታታ ውጤት እንደሆነ አስረድተዋል።

አንዳንድ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ከሕገ-ወጦች ጋር በመመሳጠር የሀገር ሐብት እንዲባክን እና ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታጣ ለማድረግ እየሞከሩ እንደሚገኝ በጥናት መረጋገጡን አንስተዋል፡፡

ከፌዴራል ፖሊስ እና ከመረጃና ደኅንነት ጋር በቅንጅት በተሠራ ሥራም በሕገ-ወጥ ተግባሩ ላይ የተሰማሩትን 15 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውንና ጉዳዩ በመጣራት ላይ እንዳለ አብራርተዋል፡፡

በቀጣይም እንዲህ ዓይነት ሕገ-ወጦችን ለማሥቆም እና ወደ ሕግ ለማቅረብ ከኅብረተሰቡ እና ከሚመለከታቸው የሕግ አካላት ጋር በመቀናጀት መሥራት እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.