የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በ2016 ዓ.ም አጋማሽ በሁሉም ክልሎች ይጀመራል -መስፍን አርአያ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በ2016 ዓ.ም አጋማሽ በሁሉም ክልሎች እንደሚጀምር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ሰብሳቢ መስፍን አርአያ(ፕ/ር) አስታወቁ፡፡
በምክክሩ 600 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉ ሲሆን÷ በእስከአሁኑ ሂደት በአምስት ክልሎች እና በአንድ ከተማ አስተዳደር ተሳታፊዎች መለየታቸው ተገልጿል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ መስፍን አርአያ(ፕ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ ኮሚሽኑ በተዘዋወረባቸው ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በእያንዳንዱ ወረዳዎች 450 ተሳታፊዎች እና ዘጠኝ ባለድርሻ አካላት ተለይተዋል፡፡
የሲዳማ እና ሀረሪ ክልል እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ልየታን አጠቃለው ወደ ቀጣይ ምእራፍ መሻገራቸውንም አንስተዋል፡
ኮሚሽኑ ተሳታፊዎችን እስከ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ለመለየት እቅድ ቢይዝም በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን ነው ዋና ሰብሳቢው የተናገሩት፡፡
አጀንዳ የማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተው በቀጣይ ጊዜያት በአፋር፣ ሶማሌ ፣አማራ ፣ኦሮሚያ ፣ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሳታፊዎች ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
በአልማዝ መኮንን