ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የተደረገው የታክስ ማሻሻያ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል – የቻይናው ቼሪ ኩባንያ ስራ አስፈጻሚ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችያደረገው የታክስ ማሻሻያ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የቻይናው ቼሪ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አምራች ኩባንያ ስራ አስፈጻሚ ጄን ቹዪ ተናገሩ።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከዋና ስራ አስፈጻሚው ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ወቅትም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ተሽከርካሪ አምራቾች መዳረሻ የሆነችበትን ምክንያት አንስተዋል።
አያይዘውም በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን ፍላጎት በመጥቀስ በኢትዮጵያ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ መገንባት ለሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በመንግስት የተደረጉ ማሻሻያዎችን በተመለከተ አብራርተዋል።
የኩባንያ ስራ አስፈጻሚ ጄን ቹዪ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በማንሳት፥ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ለፍላጎቱ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
የተደረገው የታክስ ማሻሻያም ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑን ጠቅሰው፥ ኩባንያቸው የዚህ ማሻሻያ አካል ይሆናል ማለታቸውን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።
ኩባንያው በቅርቡ የቢዝነስ ተወካዮቹን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመገምገም የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ መገንባት የሚችልበትን አማራጭ እንደሚመለከት አስረድተዋል።