Fana: At a Speed of Life!

የማሕበራዊ ሚዲያ ቁማርተኞች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግስት አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሠራዊት የአማራ ሕዝብ ጠላት አድርገዉ የሚቀሰቅሱ ጽንፈኞችና በሰዉ ህይወት በመነገድ ኪሳቸዉን የሚያደልቡ የማኅበራዊ ሚዲያ ቁማርተኞች ከድርጊታቸዉ እንዲቆጠቡ መንግስት አሳሰበ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ የመከላከያ ሠራዊት የአማራ ክልልን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ከየትኛዉም አካባቢ በላይ መስዋዕትነት መክፈሉና ዛሬም ጭምር እየተዋደቀ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የትኛዉንም አካል ያለውን ጥያቄና ፍላጎት በሰላማዊ መንገድ ማቅረብና ለመፍትሄ መወያየት እንዲችል ትክክለኛ አማራጭ መንገድ መንግስት ዘርግቶ እያለ የግል ፍላጎትና ጥቅም በሃይል ለማሳካት የሚደረግ የትኛዉም ዓይነት ድርጊትና እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለውም ነው ያብራሩት፡፡

በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ጥያቄዎችና ፍላጎቶችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችል መሰረት መጣሉና ለአንዱ ተመልሶ ለሌላኛዉ የተከለከለ ጉዳይ እንደሌለም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በዚህም በስክነትና የወል እዉነቶች ላይ በመቆም ብቻ የተናጠል ጉዳዮች መፍትሄ እንደሚያገኙ መረዳት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በደቦ፣ በግርግርና በማህበራዊ ሚዲያ ጋጋታ የትኛዉም ዓይነት ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ እንደማይችልም ነው የተናገሩት ሚኒስትሩ፡፡

በመሆኑም ሠራዊታችን የአማራ ሕዝብ ጠላትና ጥቅሙን የማያስከብር አድርገዉ የሚቀሰቅሱ ጽንፈኞችና በሰዉ ህይወት በመነገድ ኪሳቸዉን የሚያደልቡ የማኅበራዊ ሚዲያ ቁማርተኞች ከድርጊታቸዉ መቆጠብ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

መላዉ የክልሉ ሕዝብም ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ከዘራፊዎችና ሽፍቶች መጠበቅ አለበትም ነው ያሉት፡፡

አክለውም ፥ በተሳሳተ መንገድ ተነሳስተዉ የሠራዊቱን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማስተጓጓል የሚጥሩ ሃይሎችም ቆም ብለዉ ማሰብ ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አሉባልታና የተሳሳቱ መረጃዎችን በመርጨት እንዲሁም የሠራዊቱን እንቅስቃሴ በማደናቀፍ በክልሉ ዉስጥ ለሚፈጠረዉ ቀዉስ እነዚህ ሃይሎችና እነሱ ያሰማሯቸዉ ቡድኖች መሆናቸዉን ከወዲሁ መገንዘብ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.