Fana: At a Speed of Life!

 በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል በዘርፉ ያለውን ኢንቨስትመንት ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢሲ) አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን የአፍሪካ ሀገራት ለዘርፋ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት ማስፋት እንዳለባቸው የአፍሪካ ህብረት ገለፀ፡፡

የህብረቱ የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚና የዘላቂ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ በኬንያ ናይሮቢ የሚካሄደውን አህጉራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸው በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ጫና እያደረሰ እንደሚገኝ እና በዚህም የተነሳ አፍሪካውያን ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን አንስተዋል፡፡

ይህንን ክስተት ለመቀልበስ የአፍሪካ ሕብረትና አባል ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየሰሩ መሆኑን አመላክተዋል።

የአፍሪካ ሀገራት አሁን ላይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በዘርፋ የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ከአጠቃላይ በጀታቸው በአማካይ 2 በመቶ መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ÷ ችግሩን በአግባቡ ለመቅረፍ በጀቱ ቢያንስ 10 በመቶ መድረስ እንዳለበትም አፅዕኖት ሰጥተዋል።

አፍሪካ የካርበን ልቀቷን ሳትጨምር ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አሟጣ በመጠቀም አህጉሪቱ አሁን ላይ ድህነትን ጨምሮ የሚገጥሟትን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ፈተናዎች ማለፍ ትችላለች ብለዋል፡፡

ይህም አህጉሪቱ አየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርገው ድጋፍ ላይ ያላትን ተስፋ በራሷ አቅም ችግሯን ለመፍታት ያስችላታል ነው ያሉት ኮሚሽነሯ።

35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ስብሰባ ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ይካሄዳል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.