Fana: At a Speed of Life!

የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከጷጉሜን 3 እስከ 5 ብሄራዊ የፀሎት እና የንስሃ መርሐ ግብር ማዘጋጀቱን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከጷጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የሶስት ቀናት ብሄራዊ የፀሎት እና የንስሃ መርሃግብር ማዘጋጀቱን ገለፀ።

መርሐ ግብሩ ‘ጥላቻ የራቀበት የፍቅር ብሩህ ተስፋ የሚታይበትን አዲስ አመት እንቀበል’ የሚል መርህ እንደሚኖረውም  ተገልጿል፡፡

የፀሎት እና የንስሃ መርሐ ግብሩ ይቅር በመባባል የጋራ አካባቢ እና ሀገር መገንባት እንዲያስችል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሀፊ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተናግረዋል።

መርሐ ግብሩ የሚከናወነው እንደየቤተእምነቱ አስተምሮ እና ስርዓት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ጷጉሜን 3 በእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስር ባሉት ሁሉም መስኪዶች የፀሎት ስነ-ስርዓት የሚደረግ ሲሆን÷ ጷጉሜን 4 በኢትዮጵያ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት የፀሎት ስነ-ስርዓት የሚደረግ ይሆናል ተብሏል።

ጷጉሜን 5 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ህብረት፣ በመካነየሱስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን የፀሎት እና የትምህርት መርሐ ግብር እንደሚኖርም ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ጷጉሜን 5 ከሰዓት በኋላ በወዳጅነት አደባባይ የሁሉም ቤተ-እምነት አባቶች እንዲሁም አማኞች እና የመንግስት አመራሮች በተገኙበት የማጠቃለያ የፀሎት መርሐ ግብር እንደሚኖር ተመላክቷል።

የሚያጋጩ ጉዳዮችን በመለየት እልባት መስጠት፣ ከልዩነት ጋር በሰላም የሚኖር ትውልድ መፍጠር እንዲሁም የጠብ እና የግጭት ምክንያቶችን መቀነስ ማስቻል ከመርሐ ግብሩ የሚጠበቅ ውጤት ነው ተብሏል።

መርሐ ግብሩ በሚደረግባቸው ቀናቶች በመፀለይ ይቅር በመባባል መጪውን ዘመን መቀበል እንደሚገባ በሐይማኖት አባቶቹ ጥሪ ቀርቧል።

በዘረያዕቆብ ያዕቆብ እና ሜሮን ሙሉጌታ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.