በአፋር ክልል ለ3 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ በ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ ለ3 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታወቀ።
የትምህርት ቁሶች ድጋፉ ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ዲቬሎፕመንት ከተሰኘ ድርጅት የተገኙ መሆናቸውም ተመላክቷል።
በዛሬው ዕለት በሠመራ ከተማ ለሚገኘው መግሊኪቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ድጋፍ ለሚያሻቸው 684 ተማሪዎች ድጋፉ መሰጠቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በክልሉ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ኡመር መሐመድ÷ ድርጅቱ ደብተር፣ እስክርቢቶና ቦርሳን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት መሳሪያዎችን ድጋፍ በማድረግ ማገዙን ተናግረዋል።
በዚህም በክልሉ ባሉ 14 ወረዳዎች ለ3 ሺህ ተማሪዎች የሚሆን ድጋፍ መለገሱን የገለጹት አቶ ኡመር÷ የትምህርት ቁሳቁሱ ዋጋቸው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መሆኑንም አመልክተዋል።
ድጋፉ በዋናነት ወላጆቻቸው አቅም ለሌላቸው የቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡