Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት ትሰጣለች – አቶ ደመቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌበር ጋር መክረዋል።

ልዩ መልዕክተኛዋ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን የአውሮፓ ህብረት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለው ግንኙነት መደበኛ እንዲሆን አዲስ መሰረት መጣሉን የጠቀሱት አኔት ዌበር፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያደረጓቸውን ውጤታማ ግንኙነቶች አድንቀዋል።

አክለውም፥ የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ ያለውን ፍላጎትም ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልፀው፤ መንግስትም ትብብሩን ለማደስና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ብሔራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትህ ያሉ ሀገራዊ አሠራሮች መተግበሩ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ እንደሆኑ ማንሳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.