Fana: At a Speed of Life!

ዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የታክስ አስተዳደር ለማዘመን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የታክስ አስተዳደር ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ዓለም ባንክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር እና የዓለም ባንክ ከፍተኛ አመራሮች “የኢትዮጵያን የታክስ አስተዳደር በማዘመን ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት” በሚል ማዕቀፍ በሚተገበር ፕሮጀክት ላይ መክረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ያለውን ጥምርታ ለማሳደግ ያግዛል መባሉን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያን የታክስ ፖሊሲ መሠረት በማድረግ የሪፎርም ሐሳቦችን የማመንጨት፣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ተደራሽ የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በቴክኖሎጂ የማሳለጥ እንዲሁም ለታክስ ከፋዮች የሚሰጡ አገልግሎቶች የጥራት ደረጃዎች የማሻሻል እርምጃዎችን ያካትታል ፕሮጀክቱ፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ፕሮጀክቱ በየደረጃው በሚገኙ የታክስ ሰብሳቢ አደረጃጀቶች ላይ በወጥነት መተግበር አለበት ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማዎች ከኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድና የመካከለኛው ዘመን (2016-2018) የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ጋር መጣጣም እንዳለበትም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.