በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ተማሪ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃናን ናጂ አሕመድ የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የክሩዝ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ የሆነችው ሃናን ናጂ በተፈጥሮ ሳይንስ 649 ውጤት በማስመዝገብ ነው ከዘንድሮ ተፈታኞች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው፡፡
ተማሪ ሃናን ናጂ አሕመድ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቧ መደሰቷን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጻለች፡፡
ለፈተናው ልዩ ትኩረት በመስጠት ቀድማ አስፈላጊውን ዝግጅት እድርጋ እንደነበርም ተናግራለች፡፡
የክሩዝ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ጀማል እድሪስ በበኩላቸው ተማሪ ሃናን ከታች ክፍል ጀምራ ጎበዝና ታታሪ እንደነበረች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም 9ኛ ክፍል 97፣ 10ኛ ክፍል 98፣ 11ኛ ክፍል ደግሞ 99 አማካኝ ውጤት ማስመዝገቧን አስታውሰዋል፡፡
በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን 356 ሺህ 878 የተፈጥሮ ሳይንስ እና 488 ሺህ 221 የማህበራዊ ሳይንስ በአጠቃላይ 845 ሺህ 188 ተማሪዎች መውሰዳቸው ይታወቃል፡፡
ከ488 ሺህ 221 የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች መካከል የማለፊያ ውጤት ያመጡት 8 ሺህ 250 ብቻ መሆናቸው ተገጿል፡፡
በሌላ በኩል ከ356 ሺህ 878 የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች 22 ሺህ 974 ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት አምጥተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ