Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ በሳይንስ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉበት አግባብ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ከሳዑዲ አረቢያ የዲጂታል አስተዳደር ባለስጣልጣን ገዢ አህመድ አልሳዋን (ኢንጂነር) ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እና በቀጣይ አመት በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ዝግጅትን በተመለከተ ምክክር አድርገዋል፡፡

በዚህ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ስለ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የትኩረት መስኮች አብራርተዋል።

የሳዑዲ አረቢያ የዲጂታል አስተዳደር ባለስጣልጣን ገዢ አህመድ አልሳዋን በበኩላቸው÷ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ሳዑዲ አረቢያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ በኤሌክትሮኒክስ መንግስት አገልግሎት፣ በተቀናጀ ዲጂታል መታወቂያ፣ በትምህርት፣ ጤና፣ የሰው ሃብት፣ ኢ-ኮሜርስ፣ ዲጂታል ኮርት እና የመረጃ መረብ ደህንነት ላይ የተሻለ ልምድ እንዳላት ገልፀዋል፡፡

ሳዑዲ አረቢያ በቀጣይ አመት ዓለም አቀፉን የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ እንደምታስተናግድ የገለፁት ገዥው ÷ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ከኢትዮጵያ ልምድ እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የትብብር መስኮችን በመለየት በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን ከኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.