የአፍሪካ መሪዎች ለአህጉራዊ ችግሮች አህጉራዊ መፍትሄ ሊያዘጋጁ ይገባል – ኦባሳንጆ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ መሪዎች ለአህጉራዊ ችግሮች አህጉራዊ መፍትሄ ሊያዘጋጁ ይገባል ሲሉ የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ተናገሩ፡፡
ኦባሳንጆ ይህንን የገለፁት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ የተማሪዎች እና የወጣቶች ልዑካን ቡድን በኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ፕሬዝዳንት ቤተ መፃህፍት ጉብኝት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡
በወቅቱ ኦባሳንጆ ባደረጉት ንግግር÷ በአፍሪካ ውስጥ ሊፈታ የማይችል እና ከአፍሪካውያን አቅም በላይ የሆነ ችግር የለም ብለዋል፡፡
አፍሪካውያን ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች የውስጥ መፍትሄዎችን በመንደፍ እና በመተግበር ሊፈቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በህዋሃት እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለመፍታት የአፍሪካ ህብረት አህጉራዊ መፍትሄዎችን ሲያፈላልግ እንደነበር እና በመጨረሻም በአህጉራዊ ማዕቀፍ ችግሩ መፈታቱን አስታውሰዋል፡፡
ከፕሪቶሪያው ስምምነትም በአፍሪካ ውስጥ የሚፈጠሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች በአፍሪካውያን መፈታት የሚችሉ መሆኑን ተምረንበታል ማለታቸውን ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡