Fana: At a Speed of Life!

ቱርክ ከአፍሪካ ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር ታደርጋለች – ኤርዶሃን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቱርክ ከአፍሪካ ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር እንደምታደርግ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ገለጹ፡፡

ኤርዶሃን በ4ኛው የአፍሪካ -ቱርክ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የቱርክ ባለሃብቶች በአፍሪካ የሚያደርጉት ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከ10 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደደደረሰ ጠቅሰዋል።

የቱርክ ኩባንያዎች በአፍሪካ ወሳኝ በሆኑ በኃይል፣ በምግብና ግብርና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማከናወናቸውንም ነው ያብራሩት።

ቱርክ እና አፍሪካ ላለፉት 20 ዓመታት ግንኙነታቸው እየጠነከረ በመምጣቱ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ትኩረት እንዲደረግ ጠይቀው፤ ቱርክ የአፍሪካን ስኬት እንደራሷ ስኬት እንደምትቆጥረው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከመጀመሪያው ጀምሮ የአፍሪካ ህብረት የቡድን 20 አባልነትን ሙሉ በሙሉ ደግፈናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በቅርቡ በሕንድ ኒውደህሊ በተካሄደው የቡድን 20 የመሪዎች ጉባዔ ላይ አፍሪካን በአባልነት መቀበሉ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

በአፍሪካ ያለው የነጻ ንግድ አካባቢ በሚቀጥሉት ጊዜያት ለንግድ እና ኢንቨስትመንት ትልቅ ዕድሎችን ይፈጥራል ሲሉም ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን የዘገበው ቲ አር ቲ ነው።

የቱርክ የንግድ ሚኒስትር ኦሜር ቦላት እንዳሉት፥ ፎረሙ በቱርክ እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚና የንግድ ግንኙነት ለማሻሻል እንዲሁም አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለመለየት እድል ይሰጣል።

ቦላት አክለውም፥ “ባለፉት 20 ዓመታት በአፍሪካ ብዙ ጉብኝቶችን አድርገናል፤ በሀገራችን ብዙ አፍሪካውያን ወዳጆቻችንን አስተናግደንና የነበረንን ግንኙነት ይበልጥ አስፍተን ከቀን ወደ ቀን እያሳደግን ነው” ብለዋል።

የአፍሪካ ቢዝነስ ካውንስል ኃላፊ አማኒ አስፉር፥ አፍሪካ ከቱርክ ጋር ያላትን ትብብር በአህጉሪቱ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲታይ እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት፣ የቱርክ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ቦርድና የቱርክ ንግድ ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁትከሐሙስ የጀመረው የሁለት ቀናቱ መርሐ ግብር የተለያዩ ምክክሮች የተካሄዱበት ነው ተብሏል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.