በመዲናዋ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተመረቁ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ ዘጠኝ የአስልፓት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ፡፡
ከተመረቁት የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል÷ የቦሌ ሚካኤል ተሻጋሪ ድልድይ፣ ከአራራት ሆቴል – ኮተቤ ኮሌጅ፣ ከኮተቤ ኮሌጅ – ካራ (ሎት2)፣ ከቄራ ከብት በረት – ጎፋ መብራት ኃይል፣ ከቀጨኔ – ቁስቋም፣ ሰሚት 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ አያት 2 የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ አያት መሪ ሳይት 4 ን ጨምሮ ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት÷ የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመትና እስከ 43 ሜትር የጎን ስፋት አላቸው፡፡
የመንገዶቹ ግንባታ መጠናቀቅም÷ የትራፊክ ፍሰቱን በማሳለጥ፣ የጉዞ ጊዜንና ወጪን በመቀነስ፣ የከተማውን ገፅታ በመቀየር እንዲሁም የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ዓይነተኛ ሚና አለው ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡
በተጨማሪም የመንገድ ደኅንነትን በማረጋገጥ እና የከተማውን የማኅበራዊ መስተጋብር በማሻሻል ብሎም ኢኮኖሚውን በማነቃቃት የግንባታዎቹ መጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ነው የገለጹት፡፡
ፕሮጀክቶቹ÷ ጀምሮ የመጨረስ፣ በገባነው ቃል መሰረት የማገልገል እና የሕዝባችንን ጥያቄዎች በተጨባጭ እየመለስን መሆናችንን የሚያሳዩ ናቸው ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡