ሚኒስቴሩ ከከተሞች ትብብር መድረክ ጋር ስምምነት ፈረመ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ከከተሞች የትብብር መድረክ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የትብብር ማዕቀፍ ሠነድ ዛሬ ፈርሟል፡፡
ስምምነትቱን የፈረሙት÷ የከተማ አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን እና የከተሞች ትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አንዷለም ጤናው ናቸው፡፡
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በፊርማ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የከተማ አጀንዳ በይበልጥ እንዲታይና በከተሞች ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ብሎም በቅንጅት ለመስራት ሕጋዊ ማዕቀፎችን መከተል ይገባል ብለዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ዛሬ የተፈረመው የስምምነት ሠነድ መዘጋጀቱን ጠቁመው÷ በርካታ የከተማ አጀንዳዎችን ለማስፈጸም ከከተሞች ትብብር መድረክ ብዙ ይጠበቃል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ ላይ በማተኮር ከተሞች ጽዱ፣ ውብና ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ብሎም ሁሉን አካታች እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ አቶ ፈንታ ተናግረዋል፡፡
አቶ አንዷለም በበኩላቸው የከተሞች የትብብር መድረክ ከዓለም ተቋማትና ከሀገር ውስጥ ከተሞች ጋር ተቋማዊ ትስስርን በመፍጠር አዳዲስ ከንቲባዎች ሲሾሙ የትውውቅ ማዕከል ሆኖ ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡