ቬንዝዌላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገሪቱ በረራ እንዲጀምር ጥሪ አቀረበች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቬንዝዌላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገሪቱ በረራ እንዲጀምር ጥሪ አቅርባለች፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቬንዝዌላ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቫን ጊል ፒንቶ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ በሀገራቱ የሁለትዮሽ እና ዘርፈ ብዙ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
አቶ ደመቀ ኢትዮጵያና ቬንዝዌላ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊ እና ባህላዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
ቬንዝዌላ ለኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ስታደረግ ለቆየችው ያልተቋረጠ ድጋፍም አቶ ደመቀ አመስግነዋል፡፡
ቫን ጊል ፒንቶ በበኩላቸው÷ ቬንዝዌላ በግብርና፣ በቱሪዝ እና በጤና ዘርፎች በከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቬንዝዌላ በረራ እንዲጀምር ጥሪ ማቅረባቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡