Fana: At a Speed of Life!

ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ 28 ግለሰቦች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ 28 ግለሰቦች ላይ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ፈቀደ።

ከደላላ ጋር በመመሳጠር ከህግ ውጪ በጉቦ ለውጭ ዜጎች ፓስፖርት በመስጠት፣ ዜጎችን በህገወጥ መንገድ ከሀገር በማስወጣት ወንጀል የተጠረጠሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ገምበታን ጨምሮ 28 ግለሰቦች ላይ ነው ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ የ14 ቀን ጊዜ የተፈቀደው።

ተጠርጣሪዎቹ በትናንትናው ዕለት በነበረ ቀጠሮ ለሁለተኛ ጊዜ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ከዚህ በፊት በተሰጠው 14 ቀናት ውስጥ የሰራውን የምርመራ ውጤትና ቀረኝ ያላቸውን የምርመራ ስራዎችን አብራርቶ አቅርቦ ነበር።

በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል ደግሞ የፖሊስ የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄን በመቃወም ክርክር ተደርጓል።

የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲፈቀድ ጥያቄ አቅርበው ክርክር ተደርጎበት ነበር።

ግራ ቀኙን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ የተከናወኑ እና ቀሪ ስራዎች ተብለው የቀረቡ ነጥቦችን መርምሮ በይደር ዛሬ ትዕዛዝ ለመሰጠት ለዛሬ በቀጠረው መሰረት በጽ/ቤት ብይን ሰጥቷል።

ከቀሪ ሰራዎች አንጻር ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ምርመራው ሊደናቀፍ ይችላል የሚለውን ግምት በመያዝ እና የምርመራውን ውጤታማነት ታሳቢ በማድረግ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ አለመቀበሉን ፍርድ ቤቱ አስታውቆ፤ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ለፖሊስ ፈቀዷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች ከሆኑት መካከል አንዱ ዳኞች በችሎት ለምን እንዳልተሰየሙና በጽ/ቤት ብይን ለምን እንደተሰጠ በጽሁፍ ማብራሪያ ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል።

በታሪክ አዱኛ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.