Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን  ገንዘባችንና ጉልበታችን በመጠቀም በመተባበር መከላከል ይገባል- ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 13፣2012 (ኢፍ.ቢ.ሲ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የኮቪድ- 19 ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ገንዘባችንና ጉልበታችን በመጠቀም በመተባበር መከላከል ይገባል ሲሉ ገለጹ።
 
ወይዘሮ አዳነች ይህንን የተናገሩት ሰይድ ያሲን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ያበረከተውን የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በተረከቡበት ወቅት ነው።
 
ወይዘሮ አዳነች ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ድጋፉ በሽታውን ለማከላከል ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል። ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ኢድ አል ፈጥር (ረመዳን) በዓል ዋዜማ እንኳን አድረሳቹሁ ብለዋል።
 
አያይዘውም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን እና በሽታው እያስከተለ ያለው ጉዳት ዘርፈ ብዙ እንደመሆኑ ምላሹም ዘርፈ ብዙ መሆን እንደሚገባው አስረድተዋል።
 
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በባህሪው ልዩና ተለዋዋጭ በመሆኑ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ብሎም ለመቀነስ ከትንሽ እስከ ትልቅ በመተጋገዝ፣ በመተሳሰብ እና ያለንን በማካፈል በዚህ ወቅት ኢትዮጵያዊ እሴታችንን ማጠናከር ይገባልም ነው ያሉት ።
 
በሌላም በኩል በማረሚያ ቤቶች በተሰራው ጠንካራ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን የመከላከል ስራ እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት በኮሮና ቫይረስ የተያዘ አካል አለመኖሩን ነገር ግን በልደታ አካባቢ በሚገኘዉ ጊዜያዊ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ሥፍራ (ፖሊስ ጣቢያ) የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸዉን አንስተዋል።
 
ስለሆነም ወረርሽኑ እንዳይስፋፋ ተጨማሪ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ስፍራዎችን በማዘጋጀት የተጠናከረ ስራ መሰራት እንደሚገባም ነው የገለጹት።
 
ወረርሽኙ ከተስፋፋ መቋቋም ስለማይቻል ቸልተኝነትን በማስወገድ በገበያ ቦታ፣ በእምነት ተቋማት፣ በፖሊስ ጣቢያዎች እና ሰዎች በብዛት ከሚገኙበት አካባቢ ራስን በመጠበቅ ለጤናችን ቅድሚያ በመስጠት ወረርሽኙን መካላከል እና የሚሠጠው ድጋፉም ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ማለታቸውን ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.