Fana: At a Speed of Life!

አቶ እንዳሻው ጣሰው በቅበት ከተማ በጸጥታ ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በስልጤ ዞን ቅበት ከተማ ከዚህ ቀደም ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ጎብኝተዋል፡፡

አቶ እንዳሻው በቅበት ከተማ በተፈጠረው ችግር ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው የነበሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወደ አካባቢያቸው መመለሳቸውን በጎበኙበት ወቅት÷ መቻቻል፣ አብሮነት እና አቃፊነት የስልጤ ሕዝብ መገለጫ ነው ብለዋል።

ይህን ለዘመናት የዳበረ ዕሴት ጠብቆ ማቆየት ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል የሚገኙ ታካሚዎችንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መጎብኘታቸው ተገልጿል፡፡

በከተማው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሰላማዊ መንገድ በእርቅ እንዲፈታ የሀገር ሽማግሌዎች ያደረጉት ጥረት ስኬታማ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የሀገር ሽማግሌዎች ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው በመመለስ ከዚህ ቀደም የነበረውን አብሮነት ለማስቀጠል ያደረጉትን ጥረትም አድንቀዋል።

በክርስትናም ሆነ በእስልምና እምነት ተከታዮች የደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ አሳዛኝ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት በትኩረት መሥራት ይገባል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ሀይማኖታዊ እና ፖለቲካዋ መልክ ለማስያዝ የሞከሩ አካላት መኖራቸውን ጠቁመው÷ ይህም በሰላም ወዳዱ ሕብረተሰብ ጥረት ከሽፏል ነው ያሉት፡፡

በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የጸጥታ አካላት ላደረጉት ጥረትም አመስግነዋል፡፡

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ ከድር የተለያዩ አካላት የግጭቱ መነሻ ሐይማኖታዊ ይዘት እንዲኖረው ጥረት ማድረጋቸውን ጠቅሰው÷ ለረጅም ዓመታት የቆየውን የእርስ በእርስ ትስስር ይበልጥ ለማጎልበት ይሠራል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.