Fana: At a Speed of Life!

የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ፒተር ፋሊያ የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ጎብኝተዋል፡፡

የኢፌዴሪ አየር ሃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በግዳጅ አፈፃፀሙና ተልዕኮን በብቃት በመወጣት ስኬታማ በሆነ የለውጥ ጉዞ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከዓለም በአቪዬሽን ቴክኖሎጅ የላቀ ስም ካላቸው ሀገራት አንዷ ከሆነችው የቼክ ሪፐብሊክ ጋር ተቋማዊ ትስስሮችን ለማጠናከር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።

አየር ኃይላችንም በሪፎርሙ የአቪዬሽን ትጥቆችን ለማዘመን እያከናወነ ላለው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ይረዳው ዘንድ አጋጣሚው የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማሳደግ ይረዳልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከቼክ መንግስት ጋር በተለያዩ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ተባብሮ የመስራት የረጅም ጊዜ ልምድና መልካም ግንኙነት እንዳለው አንስተዋል፡፡

በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የጀመሩትን የሰው ኃይል አቅም ስልጠና እና ሌሎች የሙያ መስኮችን ለማሥቀጠል ሁለቱ ሀገራት መስማማታቸውን የመከላከያ ሰራዊት ገጽ መረጃ ያመላክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ፒተር ፋሊያ ከቼክ ሪፐብሊክ የመጡ የአቪዬሽን ሙያተኞች ከኢትዮጵያውያን ጋር በአቪዬሽን ከባድ ጥገና ማዕከል ያከናወኑትን የአውሮፕላኖችን ዕድሜ የማራዘምና እድሳት ስራን አድንቀዋል፡፡

እንዲሁም በበረራ ትምህርት ቤት ሲሙሌተር (ምስለ በረራ) ላይ የአቅም ማሳደግ ስራዎችን በመጎብኘት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የለውጥ ጉዞ መደነቃቸውን ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.