ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለፀች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከኢትዮጵያም ሆነ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለፀች፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በጎንግ ዌቢን(ፕ/ር) ከተመራው የቻይና ብሄራዊ የአስተዳደር አካዳሚ የልዑካን ቡድን ጋር የሁለቱን ሀገራት አጋርነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
አፈ-ጉባኤ ታገሰ በውይይቱ÷ የቻይና ብሄራዊ የአስተዳደር አካዳሚ በአስተዳደር ስልጠና እንዲሁም በጥናትና ምርምር ያለውን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ያለውን ዝግጅት አድንቀዋል፡፡
አካዳሚው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አቅም ያለውና የበርካታ ምሁራን ስብስብ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተዛማጅ የሆነ ልምድ በማጋራት የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከር እንደሚገባም አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል፡፡
የቻይና ብሄራዊ የአስተዳደር አካዳሚ እና የአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ በቅርቡ የሚፈራረሙት የትብብር ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እንደሚያጠናክር መግለፃቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የቻይና ብሄራዊ የአስተዳደር አካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ጎንግ ዌቢን (ፕ/ር)፥ ቻይና ከኢትዮጵያም ሆነ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
አካዳሚው በስልጠናም ሆነ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ለኢትዮጵያ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡