Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት የትኛውንም ጉዳይ በሠላማዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት ሁልጊዜም ዝግጁ ነው – አቶ ተስፋዬ በልጅጌ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2016 (ኤ ፍ ቢ ሲ) መንግሥት የትኛውንም ጉዳይ ሠላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ለመፍታት ሁልጊዜም ዝግጁ ነው ሲሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚሰሩ የውክልና ሥራዎችን በተመለከተ የሁሉም ክልልና የከተማ መስተዳደር ተወካዮች፣ የመንግሥት ተጠሪዎች፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ተወካዮች እንዲሁም የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት ግምገማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚገልጸው ከየትኛውም ቦታ ጥያቄ አለኝ ብሎ የሚያምን አካል ካለ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን አቅርቦ በውይይት እና በድርድር ለመፍታት መንግሥት ግልጽ ፍላጎት አለው ብለዋል።
ከዚህ ውጭ ኃይልን በመጠቀም በመግደልና በመዝረፍ፣ ንብረት በማውደምና መንገድ በመዝጋት ፍላጎትን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ ህብረተሰቡ የሠላም አማራጮችን ብቻ መፍትሔ አድርገው እንዲንቀሳቀሱ ጫና ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ከፕሮጀክቶች አፈፃፀም አኳያ የትኛውንም ፕሮጀክት ጀምሮ መጨረስ የመንግሥታቸው ዋነኛ አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከለውጡ በፊት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ችግሮቻቸው እየተቀረፈ እንዲሁም አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው የሚጠናቀቁበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
የውክልና ሥራ የምክር ቤት አባላትን ከመረጣቸው የሕብረተሰብ ክፍል ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ በመሆኑ የመራጩን ሕብረተሰብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ቆጥሮ ተቀብሎ ቆጥሮ የሚያስረክብበት ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ጠቅሰው፤ ምክር ቤቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
በሕገ መንግሥቱ መሠረት የምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው የሕብረተሰብ ክፍል ጋር በዓመት ሁለቴ ተገናኝተው የሚመካከሩበትና የሚወያዩበት ሁኔታ መኖሩንም አስታውሰዋል፡፡
ይህንንም ተግባር ያለ በቂ ምክንያት በማይወጡ አባላትና የውክልና ሥራዎች እንዳይደረጉ በሚያስተጓጉሉ አካላት ላይ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.