ፈተናዎችን ወደ ምንዳ በመቀየር ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አመራሩ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ወደ ምንዳ በመቀየር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባው በብልጽግና ፓርቲ የዐቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ሙሳ አሕመድ ገለጹ፡፡
3ኛ ዙር ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙ አመራሮች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን አብርሃሞ ወረዳ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
አቶ ሙሳ አሕመድ በጉብኝቱ ወቅት÷ በውስጥ እና በውጭ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ወደ ውጤት በመቀየር ምርት እና ምርታማነትን በማሣደግ የብልጽግናን ጉዞ ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የማኅበረሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የምግብ ዋስትናን ዕውን ለማድረግ እንደሚያስችሉ ጎብኚዎች መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይ ከዕዳ ወደ ምንዳ በሚል መሪ ሐሳብ በመቱ ማዕከል ሥልጠና እየተከታተሉ ያሉ አመራሮች በኢሉ አባቦር ዞን የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅትም÷ ሀገሪቱ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሐብት እና የመልማት ዐቅም በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የአመራርነት ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በተመሳሳይ ርዕሠ-ጉዳይ በሐዋሳ ከተማ 3ኛ ዙር ሥልጠና ሲከታተሉ የነበሩ አመራሮች በሲዳማ ክልል የሚገኙ የኢንዱስትሪ ተቋማትን እና ከሌማት ትሩፋት ጋር ተያይዞ የተከናወኑ ሥራዎችን ጎብኝቷል።
በአምቦ የስልጠና ማዕከል ሥልጠናቸውን የሚከታተሉ የመንግሥት አመራሮችም በዛሬው ዕለት የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በሶማሌ ክልል በስልጠና ላይ የሚገኙ የመንግሥት አመራሮች በጅግጅጋና ፋፈን ከተሞች የሚገኙ የልማት ሥራዎችን በጎበኙበት ወቅት÷ ተስፋ ሰጭ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አይተናል ብለዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!