የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ እንደሚሰራ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ በመሆን ለመደራጀት የሚረዱ ጉዳዮችን በመለየት ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ጋር ትብብሩን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሳድግ ገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) የተመሩ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ዲኖች፣ዳይሬክተሮችና ምክትል ዳይሬክተሮች የልዑካን ቡድን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን የሪፎርምና የተልዕኮ ሥራዎች መጎብኘታቸውን የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መረጃ አመልክቷል፡፡
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ እንዳመለከተው ፥ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንትና ከፍተኛ አመራሮች በጉብኝታቸው የተቋሙን ሪፎርምና ተልዕኮ የሚያስቃኛውን ዲጂታል ኤግዚቢሽን፣ ምቹ የስራ አካባቢ ለመፍጠር የተከናውኑ ተግባራትን ጨምሮ ዘመን ተሻጋሪ ተቋም ለመገንባት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር)ና ልዑካኖቻቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባካሄደው ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በፈታኝ ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ እያለፈ ቴክኖሎጂ በመጠቀምና በማበልጸግ፤ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፤ ዘመናዊ የአሠራር ስርዓቶች በመዘርጋት፤ አጋርነትና ትብብርን በማጠናከር እንዲሁም ምቹ የሥራ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ከጉብኝታቸው እንደተገነዘቡ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በሀገሪቱ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የጀመረውን መንገድ ለማሳከት የሚያገለግል ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ግብዓት ማግኘታቸውንና ተሞክሮ መቅሰማቸውን አመልክተዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በቀጣይ በተቋም ግንባታ ረገድ በጋራ ለመሥራት የሚያግዛቸውን መስመር አጠናክረው ለመቀጠል ጉብኝቱ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር)ና የልዑካን ቡድኑ አባላት በተለይ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፤ በምርምርና ጥናት እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ በመሆን ለመደራጀት የሚረዱ ጉዳዮችን በመለየት ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሳድጉ ጠቁመዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ፥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ያደረጉት ጉብኝት ሀገራዊ ደኅንነትን በማረጋገጥ ረገድ የድርሻቸውን ለማበርከት በላቀ ደረጃ መነሳሳት ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመረጃና ደኅንነትን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ሊደግፍ የሚችል እምቅ አቅም እንዳለውም ነው የገለጹት፡፡
በተለይ ውስብስብ የሆነውን ሀገራዊ ደኅንነት የማረጋገጡን ተግባር በምርምር ሥራ፣ በቴክኖሎጂና የሰው ኃይል በማብቃት ማገዝ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ረገድ የተቋሙ የጥናትና የምርምር ማዕከል ከሆነው ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጋር በትብብር የሚሠሩ ተግባራት እንደሚጠናከሩም ነው የገለጹት፡፡