መከላከያ ሠራዊት ግዳጁን በሕዝባዊ ወገንተኝነት መንፈስ እየተወጣ ነው – ሌ/ጄ መሐመድ ተሰማ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተደድር አረጋ ከበደ እና የጎጃም ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢና የምስራቅ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ በደጋ ዳሞት ወረዳ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በደጋ ዳሞት ወረዳ በፈረስ ቤት ከተማ የፈረስ ቤት አንደኛ ደረጃ ሆስፒታልን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
በዚህም ወቅት ለሆስፒታሉ የመድሃኒት ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ÷ ከፈረስ ቤት ነዋሪዎች ጋርም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ሌ/ጀ መሐመድ ተሰማ እንዳሉት ÷ ጽንፈኞች የትግል ስልታቸውን በሕዝብ ጥያቄ ውስጥ ደብቀው የዘረፋና የስልጣን ጥማታቸውን ለማሳካት ቢጥሩም በሠራዊቱ ምት ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡
የደጋ ዳሞት ሕዝብም ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በጋራ በመቆም የተገኘው ሰላም ጠባቂ መሆን ይኖርበታል ነው ያሉት።
መከላከያ ሠራዊት ፈረስ ቤትን ጨምሮ በርካታ ወረዳዎችን በመቆጣጠር ሰላም እንዲመጣ ያደረገው ግዳጁን በሕዝባዊ ወገንተኝነት መንፈስ እየተወጣ በመሆኑ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሠራዊቱ ከራስ በፊት ለሕዝብ ደህንነት መከፈል ያለበትን ሁሉ መስዋዕትነት እየከፈለ የክልሉን ሰላም የተሟላ ለማድረግ ከሕዝብ ጋር አብሮ መስራቱን እንደሚቀጥል ማረጋገጣቻውንም የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡
የደጋ ዳሞት ወረዳና የፈረስ ቤት ነዋሪዎችም ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አካባቢው የጥፋት ሃይሎች ተልዕኮ ማስፈፀሚያ እንዳይሆን የሰላም አጋርነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ነው የጠየቁት ።